• Dutch
  • English
  • Amharic
ሚድዋይፎችን ለማሰልጠን የሚያስችል የገንዘብ እርዳታ ከቢለማ ፋውንዴሽን ተገኘ

ቢለማ ፋውንዴሽን በደቡብ ብሔርና ብሔረሰብ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የአዋላጅ ነርሶች (ሚድዋይፎች) እጥረት በሚታይባቸው ወረዳዎች ተጨማሪ ባለሞያዎችን ለማሰልጠን የሚየስችል የእርዳታ ስምምነት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር ተፈራረመ፡፡ የህዝብ ብዛት በአንፃሩ ከፍተኛና ጥቅጥቅ ያል አሰፋፈር በሚታይባቸው በሰሜናዊ እና ምስራቃዊ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች በቂ የጤና ባለሞያዎች፤ ሚድወይፎችን ጨምሮ የሚገኙበትና በስራላይ ያሉበት ቢሆንም በደቡባዊና ምዕራባዊ የክልሉ ክፍሎች ግን እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሰለጠኑ የጤና ባለሞያዎች ያሉበትና በተለይም ደግሞ በአንዳንድ ወረዳዎች የሚድዋይፈሪ ባለሞያዎች ከነአካቴውም የሌሉባቸው ናቸው፡፡ ምንም እንኳ በነዚህ የክልሉ ክፍሎች የህዝቡ አሰፋፈር የተሰበጣጠረና በአንፃሩ አነስተኛ ቢሆንም፤ በባለሞያች አለመኖር ምክያት የነፍሰጡር እናቶች የቅድመ-ወሊድና ድኅረ-ወሊድ አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኙና በዚህም የተነሳ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ የእናቶችና ህፃናት ቁጥር በእጅጉ ክፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ይህንን የባለሞያዎች ክፍተት በተለይም የአዋላጅ ነርሶችን እጥረት፤ ብሎም በዚሁ ምክንያት የሚከሰተውን ከፍተኛ የእናቶችና ህፃናት ሞት በመገንዘብ፤ ቢለማ ፋውንዴሽን የባለሞያዎች እጥረት አንገብጋቢ ሆኖ የሚታይባቸውን ዎረዳዎች ቅድሚያ በመስጠት ተጨማሪ ሚድዋይፎችን በክልሉ በሚገኙ የጤና ማሰልጠኛ ተቋማት በዲፕሎማ ደረጃ ለማሰልጠን የሚያስችል የስልጠና ወጪ በመሸፈን ክፍተቱን ለመሙላት ክፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ስልጠና ሊሳተፉ የሚችሉ እጩ ሰልጣኞች የ10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና የወሰዱና በክልሉ የጤና ማሰልጠኛ ተቋማት ገብቶ ለመማር የሚያስችል ውጤት ያላቸው መሆን እንደሚኖርባቸውም ብፕሮጀክቱ ስምምነት የመግባቢያ ሰነድና በፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ዝርዝር እቅድ (project plan) ላይ ተገልጿል፡፡

ቢለማ ፋውንዴሽን ከአጋር ደርጅቱ ሰቲችቲንግ አዶፕቴር ኤን ቭሩድቭሮው (Stichting Adopteer een vroedvrouw) ጋረ በመተባበር የስልጠና ወጪውን ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ባስጀመረው ፕሮጀክት መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በያመቱ ስድስት ሰልጣኞች ለተከታታይ ሶስት አመታት የሚሰለጥኑ ሲሆን፡ ይህ የመጀመሪያው ዙር የሚያሳየውን የአፈፃጸም ብቃት መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ስልጠናው ሊቀጥል የሚችልበትን ሁኔታ የሚመቻች መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት በተግባር ለማስፈጸም የሚያስችል የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት (MOU) ከደቡብ ብሔርና ብሔረሰብ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ጋር ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ/ም (May 19, 2014) በክልሉ ርዕሰ ክትማ ሐዋሳ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ በዚህም ስምምነት መሰረት ሠልጣኞቹ ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ በፕሮጀክት ስምምነቱ ላይ በተጠቀሰው የአገልግሎት ዘመን (ለሶስት ዓመት ሥልጠና የሶስት ዓመት የአገልግሎት ዘመን) በመንግስት ተቋማት መስጠታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ በአስፈፃሚነት የሚከታተለው መሆኑን ተገልጾ፤ በቀጣይነት ባለሞያው ቦታውን መልቀቅ ቢፈልግ የክልሉ ጤና ቢሮ ከወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በምትኩ ሌላ ባለሞያ በቦታው የሚተካ መሆኑንም ጨምሮ ተገልጿል፡፡